የቴሌኮም ልህቀት አካዳሚ የሥራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች በኢትዮ ቴሌኮም እና በቴሌኮም ልህቀት አካዳሚ የሶስት ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅዶች፣ እንዲሁም የአካዳሚው የ2013 በጀት የመጀመሪያ ግማሽ ዓመት የሥራ አፈጻጸም ላይ ታህሳስ 22 ቀን 2013 ዓ.ም አዲስ አበባ ሃያት ሬጀንሲ ሆቴል ውይይት አካሄዱ፡፡
ስብሰባው በእንኳን ደህና መጣችሁ የከፈቱት የቴሌኮም ልህቀት አካዳሚ ቺፍ አቶ አየለ አዱኛ ሲሆኑ የዕለቱን መሪ ቃል ማለትም “We Aspire to Become a Preferred Operator!” በማስተዋወቅና የስብሰባውን ዓላማና የሚጠበቀውን ውጤት፣ መርሀ-ግብሩን እንዲሁም የኩባንያውን የግማሽ ዓመት አበይት ስኬቶች አብራርተዋል፡፡
በመቀጠልም የኢትዮ ቴሌኮም የሶስት ዓመት ስትራቴጂ (እ.ኤ.አ. ከ2020 እስከ 2023) ሰነድ በተለያዩ አቅራቢዎች ተከፋፍሎ እና ዝግጅት ተደርጎበት እንዲሁም ስትራቴጂውን በመረዳት እና እሴት በመጨመር ለተሰብሳቢዎቹ ያቀረቡ ሲሆን ይህም የአቀራረብ ስልት ስትራቴጂው ላይ የእኔነት ስሜት የሚፈጥርና ይበልጥ ለመረዳት የሚያስችል የአቀራረብ መንገድ በመሆኑ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተመልክቷል፡፡
በመቀጠልም የአካዳሚው ስትራቴጂ እና ኢኒሼቲቭ እንዲሁም የመጀመሪያው አጋማሽ አበይት አፈጻጸሞች ቀርበው ውይይት የተደረገባቸው ሲሆን ለተነሱ ጥያቄዎችም ተገቢው ማብራሪያ በመስጠት የቀረቡ ገንቢ ሃሳቦች ለኩባንያውና ለልህቀት አካዳሚው በግብዓትነት ተወስደዋል፡፡
በመጨረሻም አካዳሚው ላስመዘገበው ውጤት ድጋፍ እና ሙያዊ እገዛ ላበረከቱ የውስጥና የውጭ ባለድርሻ አካላት ልባዊ ምስጋና የቀረበ ሲሆን የሥራ ኃላፊዎችና ሠራተኞቹም ኩባንያው ተመራጭ የቴሌኮም አገልግሎት አቅራቢ ለማድረግ በቁርጠኛነት እንደሚሰሩ ቃል ገብተዋል፡፡