ኢትዮ ቴሌኮም በኢትዮጵያ በፊክስድ ኔትወርክ የፋይበር ኦፕቲክስ ዘርፍ የመጀመሪያ የሆነውን የሙያ ደረጃ ካርታ (Occupational Standard Map)፣ የሙያ ደረጃ (Occupational Standard)፣ የብቃት አሃድ (Unit of Competency)፣ የምዘና መሳሪያ (Assessment Tool) ፣ እንዲሁም የምዘና ማዕከል (Assessment Center) ከኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ቴክኒክና ሙያ ትምህርት እና ስልጠና (ኢ/ፌ/ቴ/ሙ/ት/ስ/) ኤጀንሲ እንዲሁም ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሙያ ብቃት ምዘናና ማረጋገጫ ማዕከል ጋር በመሆን ሲያዘጋጅ የቆየ ሲሆን የምዘና ደረጃው የተቋምና የሀገር አቀፍ ተቀባይነት ያለው (National Standard) ሆኖ ተመዝግቧል፡፡

 

የምዘና ዝግጅቱ ዋነኛ ዓላማ የሰራተኛውን አቅም በመገንባት በራሱ የሚተማመን፣ ለስራ የተነሳሳ፤ የቴክኖሎጂ መሻሻልና ፈጠራዎችን ለማምጣት ብቁና ዝግጁ የሆነ፤ ከቴክኖሎጂ እና የስራ ሁኔታዎች ጋር ራሱን የሚያላምድ፤ ክፍተቱን በምዘና የለየና ራሱን ያበቃ፤ በሙያ ዘርፉ በሚሸፈኑ የስራ መደቦች ላይ በብቃት ለመስራት የሚችል የሰው ኃይል በመገንባት በኩል ከፍተኛ ሚና መጫወት ነው፡፡

የምዘና ደረጃው መነሻ ያደረገው በዘርፉ በተቋሙ ውስጥ ያሉትን ስራዎች በማጥናት፣ በሌሎች ሀገራት የተዘጋጁ የምዘና ደረጃዎች እንዲሁም ቀጣይ የቴክኖሎጂ ሽግግሮችን ከግምት ውስጥ በማስገባት ነው፡፡ ስራው  የተከናወነው በቴክኒክ ዘርፍ ቢያንስ የመጀመሪያ ዲግሪ የትምህርት ዝግጅት፤ በፊክስድ ኔትወርክ የፋይበር ኦፕቲክስ ዘርፍ ከ5 ዓመት በላይ የስራ ልምድና፤ በሙያው የተሻለ የስራ ብቃት ያላቸውን የኢትዮ ቴሌኮም ሰራተኞች በፕሮጀክት መልክ በማሳተፍ ነው፡፡ የምዘና ደረጃው በራስ አቅም መዘጋጀቱ በግዢ ሂደት ሊወጣ የነበረውን ከፍተኛ የዶላር ወጪ ለማስቀረት አስችሏል፡፡

ምዘናው በደረጃ ሁለት (LII) የቃልና የተግባር፣ በጀረጃ ሶስትና አራት (LIII & LIV) የፅሁፍ እና የተግባር ፈተናዎች እንዲኖሩት ተደርጎ ተዘጋጅቷል፡፡

የFiber Optics Networking የደረጃ ሁለት የምዘና ማዕከል

 

የሙያ ብቃት የምዘና ደረጃ እና የምዘና መሳሪያዎች ዝግጅት በሌሎች የቴክኒካል-ኔትወርክ ዘርፍ ላይ ላሉ ሙያዎች እንዲዘጋጅ በእቅድ ላይ ይገኛል፡፡

የሙያ ብቃት ደረጃ ዝግጅትን የሚመለከት አጭር መግለጫ ከዚህ በታች ተመልክቷል

  1. የሙያ ደረጃ ካርታ (Occupational Standard Map) ምንድነው?

የሙያ ደረጃ ካርታ የሙያ ጀረጃዎችን ስያሜ፣ የምዘና ቅደም ተከተልና የብቃት ማረጋገጫ ደረጃዎችን የሚያሳይ ነው::

  1. የሙያ ደረጃ (Occupational Standard) ምንድነው?

የሙያ ደረጃ (Occupational Standard) በተሰራው የስራ ጥናት (Job Assessment) መሰረት ተመሳሳይነት ያላቸው ስራዎች የሚጠይቁትን ችግር የመፍታት/መረጃን የማቀናበር ክህሎት (Problem Solving Capability/Information Processing) ፤ የተጠያቂነት፣ ኃላፊነትና ራስን ችሎ የመስራት ደረጃ (Level of Accountability, Responsibility & Autonomy) ፤ የዕውቀት እና ክህሎት ደረጃ (Level of Knowledge and Skill) እና የስራው ባህሪና ውስብስብነት (Level of task/operational environment) ከግምት ውስጥ በማስገባት የተደራጁ ናቸው፡፡

  1. የብቃት አሃድ (Unit of Competency) ምንድነው?

የእውቀት፣ ክህሎት እና አመለካከት ዝርዝሮች፣ ስራው የሚመዘንበትን አካሄድ፣ ስራውን ለማከናወን የሚያስፈልጉ የስራ፣ የደህንነት መጠበቂያ መሳሪያዎችን እና የመሳሰሉትን ዝርዝሮች የሚያስረዳ ነው ፡፡ ይህም ተመዛኞች ብቃታቸውን በምን ደረጃ ለማዳበር እንደሚችሉ ያመላክታል፡፡

የብቃት አሃድ (Unit of Competency) የተደራጀው ሙያው የሚያስፈልገውን የስራ ችሎታ (Task skill)፣  ስራን የማስተዳደር ችሎታ (Task management skill) ፣ ያልተጠበቀና ድንገተኛ ክስተትን የማስተዳደር ችሎታ (Contingency management skills) እና በኃላፊነት፣ በሚጠበቀው ልክና ከሌሎች ጋር አብሮ የመስራት ችሎታ (Job/Role environment) በማገናዘብ ነው፡፡

  1. የምዘና መሳሪያ (Assessment Tool) ምንድነው?

የምዘና መሳሪያ በእያንዳንዱ የብቃት አሃድ መግለጫ ውስጥ በተመለከቱት የአፈፃፀም መለኪያዎች መሰረት የተመዛኙን ብቃት በፅሁፍና በተግባር ምዘና ለመለካት የሚዘጋጅ ነው፡፡ የመመዘኛ መሳሪያው ሰነድ ምስጢራዊነትን፣ ታማኝነትን እና ተጠያቂነትን ባማከለ ተሰርቶ ለኢ/ፌ/ቴ/ሙ/ት/ስ/ ኤጀንሲ እንዲረከብ ተደርጓል፡፡

  1. የመመዘኛ ማዕከል (Assessment Cetner) ምንድነው?

የምዘና ማዕከል ተመዛኞች የተግባር ምዘና ለመውሰድ እንዲችሉ ስራቸውን የሚሰሩባቸውን መሳሪያዎች በማደራጀት የተዘጋጀ ነው፡፡