የቴሌኮም ልህቀት አካዳሚ ማኔጅመንት አባላት የኢትዮ ቴሌኮም የ2012 በጀት ዓመት አፈጻጸም፣ የሶስት ዓመት ስትራቴጂ ዕቅድ እና የ2013 በጀት ዓመት ቢዝነስ ዕቅድ ላይ እንዲሁም የአካዳሚው የ2012 በጀት ዓመት አፈጻጸም እና የ2013 በጀት ዓመት ዕቅድ ላይ ሐምሌ 29 ቀን፣ 2012 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ ውይይት አደረጉ፡፡
በመክፈቻ ንግግራቸው የቴሌኮም ልህቀት አካዳሚ ቺፍ ኦፊሰር አቶ አየለ አዱኛ በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት ከቤት ባለመውጣት ሥራቸውን በተለያዩ ቴክኖሎጂዎች በመታገዝ ሲያከናውኑ ለነበሩ የአካዳሚው አመራር አባላት እንኳን በጤናና በሰላም አገናኘን በማለት የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክታቸውን ያስተላለፉ ሲሆን በመቀጠልም የኩባንያውን የ2012 በጀት ዓመት አፈጻጸም አቅርበዋል፡፡ በዚህም ወቅት በተጠናቀቀው የ2012 በጀት ዓመት ኢትዮ ቴሌኮም የኮቪድ 19 ወረርሽኝን በመከላከል እና ተዕጽኖውን በመቋቋም ብቁ፣ ተወዳዳሪ፣ ተመራጭ እና ትርፋማ ኩባንያ ለመሆን የነደፈው ስትራቴጂ ፍሬ አፍርቶ በታሪኩ እጅግ በጣም ከፍተኛ የሆነ የ 47.7 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ ገቢ (የዕቅዱን 105.1 በመቶ) በማስመዝገቡ እንኳን ደስ አላችሁ በማለት ደስታቸውን የገለጹ ሲሆን ተሳታፊዎችም ደስታቸውን ሞቅ ባለ ጭብጨባ ገልጸዋል፡፡ አቶ አየለ ቀጥለውም ይህ ውጤት የተመዘገበው ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን በቅንጅት ተቋቁሞ ወደ መልካም አጋጣሚ መቀየር የሚችል የሰው ሃይል በመፈጠሩ እንዲሁም የደንበኞችን የቴሌኮም አገልግሎት ተሞክሮ የሚያሻሽሉ ዘርፈ-ብዙ እና መጠነ-ሰፊ ሥራዎች በመሠራታቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በመቀጠልም አቶ አየለ የኩባንያውን ሽግግር፣ እድገት እና ተስፋ የሚያመለክተውን የሶስት አመት (BRIDGE) ስትራቴጂ እና ቢዝነስ ዕቅድ ያቀረቡ ሲሆን ከዚያም በመቀጠል በኩባንያው አፈጻጸም፣ ቢዝነስ ዕቅድ እና ስትራቴጂ ላይ ውይይት ተደርጎ ከተሰብሳቢው ግብዓት ተወስዷል፡፡
በመርሃ ግብሩ መሠረት የፕላኒንግ እና ፐርፎርማንስ አሴስመንት ዳይሬክተር ማህሌት ወንድሙ የልህቀት አካዳሚውን የ2012 በጀት ዓመት አፈጻጸም ያቀረቡ ሲሆን በዚህም መሠረት አካዳሚው በገጽ ለገጽ ሥልጠና ለ12,285 (የዕቅዱን 106 በመቶ) እንዲሁም በዲጂታል ሥልጠና 5,952 ሠልጣኞችን (የዕቅዱን 192 በመቶ) ማሰልጠኑን እና በጥምር ሥልት ሥልጠና መስጠት መጀመሩን ገልጸዋል፡፡ በመቀጠልም የልህቀት አካዳሚው የ2013 በጀት ዓመት ዕቅድ ቀርቦ በዕቅድ አፈጻጸሙ እና በዕቅዱ ላይ ከማኔጅመንት አባላቱ አስተያየት እና ግብዓት ተሰጥቷል፡፡
በመጨረሻም አቶ አየለ የቴሌኮም ዘርፉ በቀጣይ ለውድድር ክፍት የሚደረግ መሆኑን ግምት ውስጥ በማስገባት ኩባንያውን ብቁ እና በደንበኞቹ ዘንድ ተመራጭ ለማድረግ የሚያስችል የሰው ኃይል በማብቃት ረገድ የአካዳሚው ሚና የላቀ በመሆኑ በ 2013 በጀት ዓመት ኮቪድ 19 የሚፈጥረውን ተግዳሮት መቀነስ የሚያስችሉ የዲጂታል ቴክኖሎጂዎችንና ሌሎች ስልቶችን በመተግበር የሚጠበቅባቸውን ሚና እንዲጫወቱ ለስብሰባው ተሳታፊዎች ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የቴሌኮም ልህቀት አካዳሚ
ነሐሴ፣ 2012 ዓ.ም