በቴሌኮም ልህቀት አካዳሚ፣ በፊክስድ ኔትወርክ ዲቪዥን እና ሁዋዌ ኢትዮጵያ በትብብር የተቋቋመው የFTTH ቤተ-ሙከራ እና የሥልጠና ክፍል በይፋ ተመርቆ አገልግሎት መስጠት ጀመረ፡፡ ይህም ሙሉ በሙሉ ፋይበር የሆነና ከፍተኛ ፍጥነት ያለው የኢንተርኔት አገልግሎት ለደንበኞች ለማቅረብ የሚያስችል ዘመናዊ የቤተ-ሙከራ እና ተግባር-ተኮር ስልጠና ለመስጠት የሚያስችል የስልጠና ክፍልን ያካተተ ማዕከል ነው፡፡
የአገልግሎት ቤተ-ሙከራው በይፋ መጀመር ኩባንያችን አስተማማኝ የኮሙኒኬሽን እና ህይወትን የሚያቀሉ የቴሌኮም ሶሉሽኖችን/አገልግሎቶችን እንዲሁም እንደ ስማርት ሲቲና ስማርት ሆም ያሉ ዓለም የደረሰበትን የዲጂታል ቴክኖሎጂዎች ለዜጎች ለማቅረብ አስቻይ ሁኔታ ከመፍጠሩም በላይ ጥራት ያለውና
አስተማማኝ የፋይበር ኔትወርክ በመዘርጋት በውድድር ገበያው ውስጥ ብቁ እና የሰለጠነ የሰው ሃይል ለመገንባት ከፍተኛ ፋይዳ እንደሚኖረው የተገለጸ ሲሆን፣ በሁለቱ
ተቋማት መካከል ያለው የመልካም አጋርነት ማሳያ መሆኑም ተብራርቷል፡፡
በፕሮግራሙ ላይ የኩባንያችን እና የሁዋዌ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የሚመለከታቸው የኩባንያችን ቤተሰቦች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችም የታደሙ ሲሆን፣ በቤተ-ሙከራው ግንባታ ላይ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ላበረከቱ የሁዋዌ ኢትዮጵያ፣ የኩባንያችን ማኔጅመንት አባላት እና ሠራተኞች የምስጋና እና የእውቅና
ሠርተፊኬት ተበርክቶላቸዋል፡፡