የቴሌኮም ልህቀት አካዳሚ (ቴ.ል.አ.) ቤተሰቦች በአካዳሚው ውስጥ ለሚገኙ ሁሉ የላቀ የቡድን መንፈስ፣ አብሮነት እና ቤተሰባዊ ትስስርን በማጎልበት የሥራ ቦታ ድባብን አስደሳችነት በመጨመር ምርታማነትን ለመጨመር በማሰብ በራስ ተነሳሽነት ያዘጋጁት ዓመታዊ የጋራ በዓል የቴ.ል.አ. ቤተሰቦች እንዲሁም በመርሃ ግብሩ ላይ የተጋበዙ በቅጥር ግቢው ውስጥ የሚሰሩ የፊዚካል ሴኩሪቲ አባላት፣ የካፊቴሪያ እና ሌሎች የኮንትራት ሠራተኞች በተገኙበት በድምቀት አከበሩ፡፡
በዝግጅቱ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የቴሌኮም ልህቀት አካዳሚ ቺፍ ኦፊሰር አቶ አየለ አዱኛ ይህን የመሰለ ደማቅ ፕሮግራም በሠራተኞች ራስ ተነሳሽነት በፍጥነት መዘጋጀቱ ያስደነቃቸው መሆኑን በመግለጽ ይህም በአካዳሚው ውስጥ በራስ ተነሳሽነት አልሞ፣ አቅዶ እንዲሁም ሪሶርስን አቀናጅቶ በቅልጥፍናና በጥራት የመተግበር አቅም መኖሩን ገልጸዋል፡፡ አቶ አየለ በመቀጠልም ይህን መሰል የአብሮነት መርሃ ግብር የአካዳሚውን ብሎም የኩባንያውን ቤተሰቦች በይበልጥ በማቀራረብ ኢትዮ ቴሌኮም በውድድር ገበያው ውስጥ ልቆ ለመቀጠል በማድረግ ላይ ለሚገኘው ፈጣን ግስጋሴ ተጨማሪ አቅምና አመቺ መደላድል የሚፈጥር ከመሆኑ በላይ ኩባንያችን ሰው ተኮር በመሆን ንቁ እና በስራ አካባቢያቸው ደስተኛ የሆኑ ሠራተኞችን ለመፍጠር ለሚያደርገው ጥረት የበኩሉን ሚና የሚጫወት መሆኑን በመግለጽ ለፕሮግራሙ አስተባባሪዎች ያላቸውን ልባዊ አክብሮትና ምስጋና አቅርበዋል፡፡
በአብሮነት መርሃ ግብሩ ወቅት የተከናወኑ የተለያዩ ቡድን መንፈስን የሚያጎለብቱ ጭውውቶች፣ አዝናኝ የሙዚቃና የውዝዋዜ ትዕይንቶች የበዓሉን ድባብ ላይ ድምቀት የጨመሩ ሲሆን በዚሁ ወቅትም አዳዲስ ዲቪዥኑን የተቀላቀሉ ሠራተኞችም የትውውቅና ኬክ ቆረሳ ፕሮግራም አከናውነዋል፡፡
የአብሮነት መርሃ ግብሩ ከዕቅድ፣ ከበጀት፣ ከምግብ ዝግጅት እስከ አጠቃላይ መስተንግዶ ድረስ በአካዳሚው ቤተሰቦች የተከናወነ መሆኑ ፕሮግራሙን ይበልጥ አቀራራቢ፣ ቤተሰባዊና አስደሳች ያደረገው ሲሆን በጋራ በዓሉ ማጠናቀቂያ ላይ ታዳሚዎች በሰጡት አስተያየትም የአብሮነት መድረኩ በደመቀ ሁኔታ ከመከበሩ ባሻገር ፕሮግራሙ በማኔጅመንቱና ሠራተኞች እንዲሁም በመላው የግቢው ማህበረሰብ ዘንድ የፈጠረው የርስ በርስ ተግባቦት እና የወዳጅነት ስሜት የኢትዮ ቴሌኮምን መሪ የእድገት ስትራቴጂ 2025 ስትራቴጂ በጋራ ለማሳካት መደላደል የሚፈጥር በመሆኑ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አጽንኦት ሰጥተዋል።
የቴሌኮም ልህቀት አካዳሚ
ሰኔ 2015 ዓ.ም.