ኢትዮ ቴሌኮም የሰራተኞቹን የሥራ ቦታ ደህንነት እና ጤንነት ለመጠበቅ ትኩረት በመስጠት የተለያዩ ስትራቴጂዎችን ተግባራዊ በማድረግ ላይ የሚገኝ ሲሆን ከዚሁ ጋር በተያያዘ በቴሌኮም ልህቀት አካዳሚ (ቴ.ል.አ.) እና በሰው ኃይል ዲቪዥን ትብብር የተዘጋጀው Ethio telecom Cares for You (Environmental & Occupational Health & Safety-EOHS) የተሰኘ የገጽ ለገጽ ሥልጠና ለፊክስድ አክሰስ ኔትወርክ (FAN) ሰራተኞች ከሰኔ 5 እስከ 13 ዓ.ም. በሶስት ዙር በቴ.ል.አ. ቅጥር ግቢ በተሳካ ሁኔታ ተሰጠ።
በስልጠናው ወቅትም በሰው ኃይል፣ የፊክስድ አክሰስ ኔትወርክ እና የቴ.ል.አ. አመራሮች መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን በዚሁ ወቅትም ኢትዮ ቴሌኮም ሰራተኞቹ የህልውናው መሠረት በመሆናቸው ደህንነቱ የተጠበቀ የስራ አካባቢ መፍጠር ቀዳሚ ተግባሩ አድርጎ እየሰራ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን ሠራተኞችም በበኩላቸው በሥራ ወቅት ከሚያጋጥም አደጋ ራሳቸውን ለመጠበቅ የደህንነት መጠበቂያ አልባሳትንና መሳሪያዎችን አጠቃቀም በተመለከተ ክህሎታቸውን እና የአጠቃቀም ባህላቸውን እንዲያሳድጉ ጥሪ ቀርቧል፡፡
የስልጠና ፕሮግራሙ በኩባንያችን የኦፕሬሽን ልህቀትን ከማምጣቱም በላይ፣ በስራ ቦታ ላይ ሊደርሱ የሚችሉትን የአካባቢና የስራ ቦታ፣ በደንበኞችም ሆነ በሰራተኞች ላይ ሊደርሱ የሚችሉ የአካል ጉዳትና የሞት አደጋዎችን ለመቀነስ የሚያስችሉ ይዘቶች፣ ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችና ጥናቶችን አካቶ እንዲሁም በተግባራዊ የመስክ ልምምዶችን ዳብሮ ለሚመለከታቸው የFAN ሠራተኞች፣ ስፔሻሊስቶች እና ሱፐርቫይዘሮችን የተሰጠ ሲሆን በቀጣይም ሥልጠናውን ለሚመለከታቸው ሁሉ በፍጥነት ለማድረስ በዲጂታል መንገድ በስፋት ለመስጠት እቅድ ተይዟል፡፡
በመጨረሻም የሥልጠናው ተሳታፊዎች በሰጡት ግብረ መልስ ሥልጠናው እውቀትና ክህሎትን በሚጨምሩ ተግባራዊ የመስክ ልምምዶች ተሰናስሎ የቀረበ በመሆኑ ለዕለት ከዕለት ስራ ጉልህ ፋይዳ ያለው እና ለሚጠበቅባቸው የደህንነት ጥንቃቄ ትልቅ እገዛና መነቃቃት እንደፈጠረላቸው እንዲሁም በስልጠናው ይዘት እና አቀራረብ እጅግ መደሰታቸውን የገለፁ ሲሆን ሌሎች የሚመለከታቸው የሥራ ጓዶቻቸው ስልጠናውን እንዲወስዱ ጠይቀዋል ።