ኢትዮ ቴሌኮም በውድድር ገበያ ቀልጣፋ የኮሙኒኬሽን እና ዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎት በመስጠት የደንበኞችን ሕይወት ለማቅለል እንዲሁም ዲጂታል ኢትዮጵያን ለማፋጠን የሚያደርገውን ጥረት ለማገዝ ከመቼውም ጊዜ በላይ የላቀ እና ቀልጣፋ የሰፕላይ ቼይን አሰራር እንዲኖረው ለማስቻል በማሰብ የቴሌኮም ልህቀት አካዳሚ (ቴ.ል.አ.) ከሰፕላይ ቼይን ዲቪዥን ጋር በመተባበር ያዘጋጀው “Building Agile Supply Chain” የተሰኘ ወርክሾፕ ከሚመለከታቸው የተለያዩ ዲቪዥኖች ተወክለው ለተገኙ የማኔጅመንት አባላት ተካሄደ፡፡
በወርክሾፑ ላይ በመገኘት የመክፈቻ መልዕክት ያስተላለፉት አቶ አየለ አዱኛ ቺፍ የቴ.ል.አ. ኦፊሰር እና ወ/ሮ በለጡ ዴላሞ ቺፍ ሰፕላይ ቼይን ኦፊሰር ሲሆኑ፣ በመድረኩ በተላለፈው መልዕክት ኩባንያችን በመላ ሀገሪቱ የሚያቀርባቸውን የቴሌኮም እና የቴሌብር ምርትና አገልግሎቶች በስፋት፣ በጥራት እና በቅልጥፍና በማቅረብ፣ የደንበኞችን ተሞክሮና እርካታ በመጨመር በውድድር ገበያው ውስጥ ልቆ ለመገኘት የሚያደርገውን ጥረት ለማስቀጠል ጠንካራ ሰፕላይ ቼይን ያለውን የማይተካ ሚና በመግለጽ፣ ጉዳዩም በሰፕላይ ቼይን ዲቪዥን ደረጃ ብቻ የሚወሰን ሳይሆን ከፕሮዳክት ዴቨሎፕመንት እስከ ደንበኞች ሽያጭ ድረስ የሚዘልቅና በዚህ ሰንሰለት የሚሳተፉ የሥራ ክፍሎችን በሙሉ የሚያካትት መሆኑ ተገልጿል፡፡
የዎርክሾፑ ዓላማ ኢትዮ ቴሌኮም የላቀ ሰፕላይ ቼይን አሰራር እንዲኖረው ማድረግ ሲሆን፣ የአጃይል ሰፕላይ ቼይንን ምንነት፣ አጃይል ሰፕላይ ቼይን ለኩባንያችን የሚኖረው ጠቀሜታ እና የሌሎች ኩባንያዎችን ምርጥ ተሞክሮ የሚሉ ይዘቶች በተለያዩ አሳታፊ በሆኑ ስልቶች በመጠቀም ለተሳታፊዎች ግንዛቤ ተፈጥሯል፡፡ በተጨማሪም የዎርክሾፑ ተሳታፊዎች ኩባንያችን አጃይል ሰፕላይ ቼይን ስትራቴጂን በመተግበር ረገድ የደረሰበትን ደረጃ በመገምገም እንዲሁም ሁሉም የሚመለከታቸው የሥራ ክፍሎች በትግበራ ረገድ ሊጫወቱት የሚገባውን የማይተካ ሚና በመለየትና በማዳበር የጋራ ግንዛቤ ፈጥረዋል፡፡
በዚህም ወቅት ከዚህ ቀደም አጃይል ሰፕላይ ቼይን ፕሮግራም በገጽ-ለገጽ ለሰፕላይ ቼይን ዲቪዥን ሠራተኞች በተከታተይ ተሰጥቶ መልካም ግብረ መልስ ተገኝቶበት የነበረ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ ይህም አጃይል ሰፕላይ ቼይን አሰራርን በሥራ ቦታ ለመተግበር አመቺ እንደሚያደርግ ግንዛቤ ተወስዷል፡፡ በመጨረሻም ተሳታፊዎች ባስተላለፉት መልዕክት በዎርክሾፑ ቆይታቸው ባገኙት እውቀት፣ ልምድ እና ተሞክሮዎች እጅግ በጣም ደስተኛ እንደነበሩ በመግለጽ የቀሰሙትን ልምድና ተሞክሮ በሥራቸው ላይ በመተግበር የኩባንያችን ሰፕላይ ቼይን ኦፕሬሽን ቅልጥፍና ይበልጥ እንዲልቅ በማድረግ በውድድር ገበያው ውስጥ ቀልጣፋ አሰራርን በማስፈን የኩባንያችንን Lead 2025 የእድገት ስትራቴጂን ለማሳካት የበኩላቸውን ጥረት ሁሉ ለማድረግ ቃል ገብተዋል፡፡