ኢትዮ ቴሌኮም በውድድር ገበያው በቴሌኮም አገልግሎት ዘርፍ ብቁ እና ተመራጭ የአገልግሎት ሰጭ ተቋም ሆኖ ለመገኘት በማከናወን ላይ ካለው መጠነ ሰፊ የቴክኖሎጂ ማስፋፋት፣ የአሰራር ሥርዓት ማሻሻል እና አዳዲስ አገልግሎቶችን የማሳደግ ሥራ በተጨማሪ መጠነ ሰፊ የአቅም ግንባታ ሥራ፣ በተለይም ከደንበኞች ጋር በቀጥታ ወይም በአገልግሎት አሰጣጡ ሂደት ለሚገናኙ የሥራ ክፍሎች በርካታ የሥልጠና ፕሮግራሞችን በመቅረፅና በመስጠት ላይ እንደሚገኝ ተገለጸ፡፡

በዚህም መሠረት በተለይ በሽያጭ ማዕከላትና በአጋሮች ዙሪያ ከጫፍ እስከ ጫፍ ባለው የአሠራር ሰንሰለት ውስጥ ተሳታፊ ለሆኑ አገልግሎት ሰጪዎች በልዩ ሁኔታ ቅድሚያ በመስጠት ተወዳዳሪነትን በሚያጠናክር መልኩ ሥልጠናዎች እየተቀረፁ በመሰጠት ላይ መሆኑ ታውቋል፡፡ ይህንኑ አጠናክሮ በመቀጠል ደንበኞቻችን ወደ ሽያጭ ማዕከሎቻችን ሲመጡ “ “ከፍትፍቱ ፊቱ” እንደሚባለው ከመግቢያ በሮች ጀምሮ በእያንዳንዷ ግንኙነታቸው መልካም የደንበኛ መስተንግዶ እንዲያገኙ ለማድረግ በማሰብ የፊዚካል ሴኩሪቲ አባላት ያላቸውን መልካም ሥነ-ምግባር የውድድር ገበያው ከሚፈልገው የደንበኞች መስተንግዶ እውቀትና ክህሎት ጋር በማቀናጀት የላቀ የደንበኛ አያያዝ ለመስጠት የሚያስችላቸውን የደንበኛ አያያዝ ሥልጠና ”Customer Handling for Security Workforce” በሚል ርዕስ በፊዚካል ሴኩሪቲ ዲቪዥን እና በቴሌኮም ልህቀት አካዳሚ ትብብር ተዘጋጅቶ መሰጠቱ ታውቋል፡፡

በሥልጠናዎቹ መክፈቻ ላይ አቶ አየለ አዱኛ የቴሌኮም ልህቀት አካዳሚ ቺፍ ኦፊሰር እና አቶ ተስፋዬ የማነ የፊዚካል ሴኩሪቲ ቺፍ ኦፊሰር ባስተላለፉት መልዕክት በአሁኑ ወቅት የፊዚካል ሴኩሪቲ አባላትን ማዕከል ያደረገ ይህን መሰል ሥልጠና እንዲሰጥ መደረጉ የፊዚካል ሴኩሪቲ አባላት የሀገር እና የተቋም ደህንነትን በማረጋገጥ በውድድር ገበያ ወቅት በደንበኛ አያያዝ በኩል የበኩላቸውን የማይተካ ሚና መጫወት እንደሚጠበቅባቸው እና የደንበኞች ተሞከሮ መልካም እንዲሆን ለማድረግ በሥልጠናው የሚያገኙትን እውቀት ካላቸው አንጋፋ የሕይወት ተሞክሮ ጋር በማዋሃድ ወደ ሥራ ቦታቸው ሲመለሱ በመተግበር ይህ ሀገራዊ ተቋም ተወዳዳሪ ሆኖ እንዲቀጥል የየበኩላቸውን ሁሉ ለማድረግ ትልቅ ኃላፊነት እንደተጣለባቸው ተገልጿል፡፡

የሥልጠና ፕሮግራሙ የፊዚካል ሴኩሪቲ አባላት በውድድር ገበያ ተመራጭ የሚያደርግ የደንበኞች አያያዝ ለማስመዝገብ ኩባንያችን በማድረግ ላይ ያለውን ዘርፈ ብዙ ጥረት የሚያግዝ ሲሆን የጥበቃ አባላቱ የኩባንያችንን ደህንነት ከማስጠበቅ በተጨማሪ ስለደንበኞች አገልግሎት አሰጣጥና አያያዝ ጽንሰ ሀሳብ በመረዳት እና በደንበኛ መስተንግዶ ሥነ-ምግባሮች ዙሪያ ተገቢውን እውቀትና ክህሎት በመታጠቅ የላቀ የደንበኞች መስተንግዶ በመተግበር በሽያጭ ማዕከሎቻችንና የሥራ ቦታዎቻችን ደንበኞች የሚኖራቸውን ተሞክሮ እና ቆይታ የላቀ በማድረግ ሁሉን አቀፍ የደንበኛ እርካታን ለማምጣት የሚያስችል ነው፡፡

በስልጠናው መጨረሻ ተሳታፊዎች በሥልጠናው ይዘትና አቀራረብ የረኩ እንዲሁም በደንበኛ አያያዝ ዙሪያ የገበዩት እውቀትና ክህሎት ለሥራቸው ትልቅ ፋይዳ ያለው መሆኑን በመግለጽ ወደ ሥራ ገበታቸው ሲመለሱ በላቀ ሁኔታ ለመተግበር ያላቸውን ቁርጠኝነት ገልፀዋል፡፡ ይህን መሰል ሥልጠናዎች በቀጣይ እንደየቅደም ተከተላቸው ለፕሪሚየም፣ ግራንድ፣ ከፍተኛ፣ መካከለኛ፣ ኪዮስክ እና ኪዮስክ ኮርነር ለሚሰሩ የፊዚካል ሴኩሪቲ ዲቪዥን አባላት ለመስጠት ዕቅድ መያዙ ታውቋል፡፡