በውድድር ገበያው ብቁና በደንበኞቹ ዘንድ ተመራጭ ሆኖ ለመቀጠል ዘርፈ ብዙ ጥረት እያደረገ የሚገኘው ኢትዮ ቴሌኮም “Enhancing Distribution Channel Operation in Competitive Market” በሚል ርዕስ ለኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት ሪጅናል ኃላፊዎችና ሠራተኞች የሰጠ ሲሆን፣ ቀደም ሲል ከኩባንያችን ጋር በኤክስክሉሲቭ ስትራቴጂክ እና ሴሌክቲቭ አከፋፋይ በመሆን ለመስራት ስምምነት ለፈጸሙ ድርጅቶች በተመሳሳይ መሰጠቱ ይታወሳል፡፡
በሥልጠና ፕሮግራሙ ላይ አቶ አየለ አዱኛ ቺፍ የቴሌኮም ልህቀት አካዳሚ ኦፊሰር እና የሴልስ ዲቪዥን የሥራ ኃላፊዎች በመገኘት መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን፣ በዚህም ወቅት ኢትዮ ቴሌኮም የውድድር ገበያውን ግምት ውስጥ በማስገባት እያከናወነ ያለውን ፈጣን የለውጥ ጉዞ በመረዳት እና የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር ያለውን ታሪካዊ ግንኙነት በማሰብ ከመቼውም በላቀ አጋርነት ለመስራት የስርጭት ስትራቴጂ እና የቢዝነስ ዕቅድ በማውጣት እንዲሁም ተገቢውን ሀብትና የሰው ኃይል በመመደብ ምርትና አገልግሎታችንን በመላ ሃገሪቱ የሚገኙ የአገልግሎት መስጫ ማዕከሎቻቸውን በመጠቀም ተደራሽ የማድረግ ኃላፊነታቸውን በልህቀት እንዲወጡ የሚያሳስብ መልዕክት መተላለፉ ታውቋል፡፡
የስልጠናው ዋና ዓላማም አጋር አከፋፋይ ድርጅቶች ኢትዮ ቴሌኮም በመላ ሀገሪቱ እያቀረበ ያለውንና ወደፊት የሚያቀርባቸውን አዳዲስ የቴሌኮም እና የቴሌብር ምርትና አገልግሎቶች በሥርጭት ቻናላቸው አማካይነት ለደንበኞች በስፋት፣ በጥራት እና በቅልጥፍና በመስጠት፤ የደንበኞችን ተሞክሮና እርካታ በመጨመር በገበያው ውስጥ ምርትና አገልግሎታችን ልቆ እንዲዘልቅ የሚደረገው ጥረት የበለጠ አጠናክሮ እንዲቀጥል ለማድረግ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡
በፕሮግራሙ ማጠናቀቂያ ላይ ሠልጣኞች በስልጠናው ዝግጅት እና አቀራረብ እጅግ የተደነቁ መሆኑን ገልጸው ያገኙትን ግንዛቤ፣ ተሞክሮዎችና አቅጣጫዎች ወደ መሬት በማውረድ እና ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር እንደ አንድ ቤተሰብ ተቀራርቦ በቀናነትና በትጋት በመስራት የኢትዮጵያን ዲጂታል ትራንስፎሜሽን ወደላቀ ደረጃ ለማሳደግ የበኩላቸውን ሚና እንደሚወጡ ቃል መግባታቸው ታውቋል፡፡