የቴሌኮም ልህቀት አካዳሚ የ5ጂ ሞባይል ኔትዎርክ ቴክኖሎጂ ሥልጠና በመስጠት ላይ ነው
ኢትዮ ቴሌኮም በውድድር ገበያ የላቀ አገልግሎት በመስጠት የደንበኞችን ፍላጎት ለማርካት እና የዲጂታል ኢትዮጵያን ዕውን ለማድረግ በሚያደርገው ጥረት የ5ጂ ኔትወርክ ቴክኖሎጂን ደረጃ በደረጃ በመተግበር በአዲስ አበባ እና በአዳማ ተግባራዊ በማድረግ እንዲሁም በሌሎች አካባቢዎች ለመተግበር መጠነ-ሰፊ ሥራዎችን በማከናወን ላይ መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን በዚህ ረገድ የተሻለ የሰው ሃብት እውቀት እና ክህሎት ለመገንባት የሚያስችል “5G NETWORK PLANNING AND OPTIMIZATION” የተሰኘ የሥልጠና ፕሮግራም አዘጋጅቶ በተለያየ ዙር በቴሌኮም ልህቀት አካዳሚ በመሰጠት ላይ ይገኛል፡፡
የ5ጂ ኔትወርክ ፕላኒንግና ኦፕቲማይዜሽን የሥልጠና ፕሮግራም እያደገ የመጣውን የደንበኞች ፍላጎት የሚያረካ እና የኢትዮጵያን ዲጂታል ኢኮኖሚ እና ቢዝነስ እንቅስቃሴን ለማላቅ እንዲሁም የማህበረሰባችን የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ላይ ከፍተኛ ለውጥ ለማምጣት በመደረግ ላይ ላለው ጥረት የሠራተኛውን ሙያዊ አበርክቶ ከፍ ለማድረግ በሚያስችል መልክ የተቀረጸ ሲሆን በ5ጂ የሞባይል ኔትዎርክ ቴክኖሎጂ ዙሪያ በቂ ክህሎት እና ግንዛቤ በማስረጽ በሰው ኃይል ረገድ ለደንበኞቻችን የላቀ አገልግሎት በመስጠት ምርጥ የደንበኞችን ተሞክሮ ለመፍጠር የሚያስችል ነው፡፡
በተጨማሪም የሥልጠና ፕሮግራሙ ዘመናችንን በፍጥነት እየቀየረ ያለውን የማሽን ከማሽን ግንኙነት እውን በማድረግ በተለያዩ የሀገራችን ኢንዱስትሪዎች ሊጫወት የሚችለውን ሚና ግምት ውስጥ በማስገባት እና ኩባንያችንም ቴክኖሎጂው ይዞት የመጣውን መልካም አጋጣሚ ለመጠቀም የነደፈውን ስትራቴጂ ለማስፈጸም የሚችል የሰው ኃይል (Human Capital) በመፍጠር ሠራተኞች ከወዲሁ ስለ አምስተኛው ኔትዎርክ ቴክኖሎጂ ምንነት፣ አርክቴክቸር፣ መመዘኛዎች /standards/፣ ስለቴክኖሎጂው ኮር፣ አክሰስ ዶሜይን፣ የዲፕሎይመንት አማራጮችን እንዲሁም የሬዲዮ ፕላኒንግ፣ ኦፕቲማይዜሽንና ትግበራ እውቀትና ክህሎት እንዲታጠቁ ያደርጋል፡፡
ሕዳር 2015 ዓ.ም.
የቴሌኮም ልህቀት አካዳሚ