የቴሌኮም ልህቀት አካዳሚ (ቴ.ል.አ.) ከሴልስ ዲቪዥን ጋር በመተባበር 36ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ እና 42ኛው የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት ጉባዔን አስመልክቶ ከተለያዩ የአፍሪካ እና የአለም ሃገራት ወደ ሀገራችን ለሚመጡ እንግዶች የቴሌኮም አገልግሎት ለመስጠት በተዘጋጁ የኢትዮ ቴሌኮም የአገልግሎት ማዕከላት አማካይነት በቴሌኮም አገልግሎት ረገድ የላቀ የደንበኞች አገልግሎት በመስጠት የኩባንያችንንና የሀገራችን ገጽታ ለመገንባት እንዲቻል ታስቦ በሁለቱ ዲቪዥኖች ትብብር የተቀረጸው “Onboarding of Ethio Telecom Service Ambassadors for 36th AU Summit” የተሰኘ የግማሽ ቀን ወርክሾፕ ለዚሁ አላማ ለተመረጡ 27 የሴልስ ዲቪዥን ሠራተኞች የካቲት 6 ቀን 2015 ዓ.ም. በቴ.ል.አ. ቅጥር ግቢ ተከናወነ፡፡

በዎርክሾፑ መክፈቻ ላይ ቺፍ የቴሌኮም ልህቀት አካዳሚ ኦፊሰር አቶ አየለ አዱኛ እና ቺፍ የሴልስ ዲቪዥን ኦፊሰር አቶ መሃመድ ሃጂ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን በዚሁ ወቅትም ተሳታፊዎቹ የህብረቱ ጉባኤ እስኪጠናቀቅ ድረስ የኩባንያችን አምባሳደር መሆናቸውን በመረዳት የተጣለባቸውን ታላቅ ተቋማዊና ሀገራዊ ኃላፊነት በታማኝነት እንደሚወጡ ያላቸውን እምነት በመግለጽ ከቀድሞው አመታት በተለየ መልክ በውድድር ገበያ ውስጥ ያለን በመሆናችን ኩባንያችን ኢትዮ ቴሌኮም በጉባኤው ተሳታፊዎች ዘንድ ተመራጭ የቴሌኮም አገልግሎት ሰጭ ሆኖ እንዲገኝ የበኩላቸውን ማድረግ እንደሚገባቸው አሳስበዋል፡፡

ዎርክሾፑ የአፍሪካ ህብረት ጉባዔው በተሳካ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ ሀገራችን የተጣለባትን ልዩ ኃላፊነት ታሳቢ በማድረግ በአየር መንገድ ቪ.አይ.ፒ. ሳሎን፣ በአፍሪካ ሕብረት አዳራሽ እንዲሁም እንግዶች በሚያርፉባቸው አስራ አንድ ባለ አምስትና ባለ አራት ኮከብ ሆቴሎች በተቋቋሙ ጊዜያዊ የኢትዮ ቴሌኮም አገልግሎት ማዕከላት ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የቴሌኮም እና የፋይናንሻል (ቴሌብር) አገልግሎቶችን ከላቀ የደንበኞች መስተንግዶ ጋር በማቅረብ የኩባንያችንን መልካም ስም ለመገንባት እንዲሁም ለጉባኤው ስምረት የዎርክሾፑ ተሳታፊዎች የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት የሚያስችሉ ግቦች ማለትም ደንበኛ ከሚጠብቀው የአገልግሎት አሰጣጥ ልኬት ልቆ መገኘት (Surpass Customer expectation)፣ መልካም ገጽታን ማሳደግ (Heighten brand reputation) እንዲሁም ሽያጭ እና ገቢ ከፍ ማድረግ ያሉት ሲሆን የጉባኤውን አውድ መረዳት እንዲሁም የቢዝነስና የግል ዝግጁነት ለማጎልበት በሚያስችል መልኩ በግሩም ቅልጥፍናና ቅንጅት የተቀረጸ ነው፡፡

በመጨረሻም ተሳታፊዎቹ ዎርክሾፑ በላቀ ሁኔታ የተዘጋጀና ከቀድሞ የአፍሪካ ህብረት ስብሰባዎች ቅድመ ዝግጅት የተለየ መሆኑን በመግለጽ ጉባዔው ከምርትና አገልግሎቶች አቅርቦት ባለፈ አህጉራዊ፣ ሀገራዊና ተቋማዊ ገፅታን ለመገንባትም ከፍተኛ አስተዋፅኦ የሚያደርግ መሆኑን ከመርሃግብሩ የተረዱ መሆኑን በመግለጽ በተቋም ደረጃ የተሰጣቸውን ይህን ታላቅ የአምባሳደርነት ኃላፊነት በታማኝነት፣ በቁርጠኝነት፣ በላቀ የደንበኛ መስተንግዶ እና ንቃት እንደሚያሳኩ እርግጠኛ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡