ከሥልጠናው ትግበራ አስቀድሞ የስልጠና ፕሮግራሞችን በመለየት የዲዛይን ሥራ የተከናወነ ሲሆን፤ የስልጠና ፕሮግራሞቹ የሞባይል መኒ አገልግሎት የግንዛቤ ማስጨበጫ፣ የሲስተም እንዲሁም ከፀደቁ የአሰራር ስርዓቶች እና ተሞክሮዎች በማዋሃድ የተዘጋጁ ናቸው፡፡ ስልጠናው ተደራሽ የሚያደርጋቸውን ባለድርሻ አካላት ታሳቢ ባደረገ መልኩ በመከፋፈል ሦስት የስልጠና አይነቶች ማለትም፤ ለውስጥና ለውጭ ኤጀንቶች፣ ለደንበኞች ሰፖርት እና ለፋይናንስ ተለይተው 32 አሠልጣኞች የአሠልጣኞች ስልጠና ከመጋቢት 9 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ እንዲወስዱ ተደርጓል፡፡
በመቀጠልም 181 እጩ አሠልጣኞች መጠነ ሠፊ ተደራሽነት ያለውን የኤጀንቶች ስልጠና ከመጋቢት 14 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ የወሰዱ ሲሆን ይህንን የአሰልጣኞች ስልጠና የወሰዱ ሠራተኞች ወደ ሥራ ቦታቸው ተመልሰው በወጣው መርኃ ግብር መሠረት ለተመረጡና ከሽያጭ ጋር ግንኙነት ላላቸው በሁሉም ሪጅኖችና ዞኖች የሚገኙ ሠራተኞችን የሚያሰለጥኑ ሲሆን ለውጤታማነቱም የአሰልጣኞች ስልጠናውን የሠጡት አሰልጣኞች በጋራ እንዲሰማሩ ተደርጓል፡፡ ለከስተመር ሰፖርት፣ ለፋይናንስ እና ለማስተር ኤጀንትሰ የሚሆኑት ስልጠናዎች ደግሞ በቴሌኮም ልህቀት አካዳሚ ውስጥ ይሰጣሉ፡፡
ይህ ይፋዊ ሥልጠና ከመጀመሩ አስቀድሞ 402 የማኔጅመንት አባላት (17 የኢትዮ ቴሌኮም ከፍተኛ አመራር ለግማሽ ቀን በገፅ ለገፅ ስልጠና፣ 301 ከተለያዩ የሥራ ክፍሎች የተውጣጡ ማናጀሮች ለአንድ ቀን በኦንላይን ስልጠና እንዲሁም 84 የሽያጭ ማናጅመንት አባላት በገጽ ለገጽ የስልጠና ዘዴዎች የአንድ ቀን ሥልጠና) ስለመሠረታዊ የኢትዮ ቴሌኮም የሞባይል መኒ አገልግሎት ምህዳር ሥልጠና ተሰጥቷቸዋል፡፡
የሥልጠና መርሃ ግብሩ ስኬታማ እንዲሆን የኩባንያው ከፍተኛ አመራር፣ ሴልስ ዲቪዥን፣ ቴሌኮም ልህቀት አካዳሚ፣ ከስተመር ኤክስፒሪያንስ እና ኳሊቲ ማኔጅመንት፣ የደንበኞች አገልግሎት፣ ፋይናንስ፣ የሰው ኃይል እና የኢንፎርሜሽን ሲስተምስ ዲቪዥኖች የላቀ ርብርብ ያደረጉ ሲሆን በመጨረሻም በሥልጠናው የተሳተፉ ሰልጣኞች የሞባይል መኒ አገልግሎትን በተመለከተ ደንበኞችን ለማገልገል የሚያስችል እውቀት እና ክህሎት የገበዩ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የቴሌኮም ልህቀት አካዳሚ
መጋቢት 2013 ዓ.ም